ወደ ይርጋለም ሲመጡ አንዳንድ ማወቅ ያለቦት ቁምነገሮች 

  • 1. ወደ ይርጋለም ሲገቡ እንግዳነቶን ይረሳሉ። የገዛ ቤቶ እንደገቡ ሰላም ይሰማዎታል። በየደረሱበት ሁሉ ዳኤቡሹ በሚል ልባዊ ሰላምታ ይታቀፋሉ። ንፁሕ፣ የዋህ የመንፈስ ፈገግታ ይመገባሉ ። ታዲያ ይርጋለም ለመክረም ሰዉ መሆኖ ብቻ በቂ ነዉ !!! 
  • 2. ለመግባባት አይቸገሩም የየትኛዉም ብሔር ቋንቋ ቢናገሩ ችግር የለም። በቻይኒኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በአረቢኛ፣ በፈረንሳይኛ መግባባት ቢፈልጉ አያስቡ ። አብዛኛዉ ሰዉ ሲዳሚኛና አማሪኛን ቅልጥፍጥፍ አድርጎ ይናገራል። መንገድ ቢጠፋቦ ሁሉም ሰዉ በንግግር ቀርቶ በምልክት ወደ ሚፈልጉት ይወስዶታል። 
  • 3. ለምንዛሪ አይጨነቁ ፣ የመንግሥትና የግል ባንኮች በተጠንቀቅ ይጠብቆታል። ገንዘቦን በኢትዮጵያ ብር በባንክና በመገበያያ ገንዘብ መመንዘር ይችላሉ ። ንግድ ፣ ዳሸን፣ ግሎባል፣ አብሲኒያ፣ ኦሮሚያ፣ አዋሽ፣ አብሲኒያ፣ ግሎባል፣ ንብ፣ ቡና …ባንኮች ሊያስተናግዶ ዝግጁ ናቸዉ። 
  • 4. ይርጋለም ቢያሻዎት በምድር ከፈለጉ በሰማይ መምጣት ይችላሉ።  ከአዲስ አበባ ወደ ሐዋሳ ለ30 ደቂቃ በአውሮፕላን ከበረሩ በኋላ ይርጋለም በመኪና ለመድረስ 30 ደቂቃ ብቻ  ይውስድቦታል። 

ከይርጋለም ሀዋሳ፣ለኩ፣ይርባ፣ሀንጠጤ፤

ከይርጋለም በቀጥታ ለኩ፤

ከይርጋለም ወንሾ እንዲሁም ፤

ከይርጋለም አለታ ወንዶ፣ ጩኮ ፣ ዲላ  በሚወስዱ መንገዶች እንደልብ መንሸራሸር ይችላሉ። 

  • 5. የእንግዳ ማረፊያ እንደልብ ነዉ ፣ ከባሕላዊ እስከ ዘመናዊ፡- ኢንጆሂ፣ ኖመነ ኖቶ፣ ፉራ፣ አረጋሽ ሎጅ ፣ ደገፋ ስሜ ሕንፃ፣ ሄርሜላ ፣ ፍርዴ ሃይሌ መታሰቢያ፣ ጊዳቦ መናፈሻ ሆቴል፣ … ማማረጥ ይችላሉ። 
  • 6. አየርዋ ሕይወት ነዉ፣ ይበርደኛል ይሞቀኛል ብለው አያስቡ። ያሻዎት ልብስ ደረብ አርገዉ ብቻ ይምጡ።  ዓመቱን ሙሉ ልምላሜና ደማቅ ብርሃን የሚያዩባት ልዩ ቦታ ናት። ለመንፈሶ እርካታ፣ ለአካሎ ደስታ ከፈለጉ ፍልውሃዎችና ፀበላት እንዲሁም ጊዳቦ፣ወይማ፣ዳማ የተባሉ ወንዞች ይጠብቆታል። 
  • 7. ደን፣ ፏፏቴ፣ ምንጮች፣ አዕዋፎት፣ አራዊት ያስደስቶታል ?!! እንግዳያዉ ወደ ይርጋለም ብቅ ይበሉና በሚያማምሩ የተፈጥሮ መልክዓ ምድሮች በቡናና የእነሰት ማሳዎች፣ በተፈጥሮ ዛፎችና በባህላዊ መንደሮች ውስጥ ይንሸራሸሩ ። ካሻዎት ታሪካዊ ቅርሶችን፣ ዋሻዎችን ጎብኝተዉ ፣አብያተክርስቲያናት ውስጥ ዉለው አድረዉ ተፈጥሯዊ ደስታን ይሸምታሉ፡፡ 
  • 8.ይርጋለም ውስጥ አስደማሚ ባሕላዊ ገበያዎች የሚቆሙባት፣ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት በተለየ ሁኔታ የሚከበርባት ከተማም ነች፡፡ የዋሻ ማርያም፣ የቅድስት አርሴማና የቅዱስ አማኑኤል  ዓመታዊ ክብረ በዓላት ፣ የዋራ ዓመታዊ ኮንፍረንስ ፣የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ ዋነኞቹ ናቸው። 
  • 9. በአሁኑ ጊዜ ሲዳማ ክልልና ይርጋለም ከተማ ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባቸው ናቸው። ሲዳማ እጅግ የከበረ የሰላምና ችግሮችን መፍቻ አፊኒ የተሰኘ ሥርዓት ያለው ሕዝብ ነው። ይርጋለም የሰላምና የሃላሌ ከተማ ናት!!! 
የማዕላዊ የሲዳማ ዞን መስተዳደር ወደ ሆነችው ውብ ከተማ ፣ ይርጋለም-  እንኳን ደህና መጣችሁ!!! 

የይርጋለም ልጆች ሴት ወንዱ በሙሉ፣

ፍቅራቸው መድሃኒት ልክ እንደ ፀበሉ። 

የበሽታን ነገር ለሀኪም ይሰጡታል ፣

የአጋንንትን ነገር ጸበል ይገቡታል፣

የይርጋለምን ናፍቆት እንዴት ያደርጉታል?! 

ዋ ይርጋለም 

የልጅነቴ ሕልም ቀለም

ዓይኔን የከፈትሽዉ ጨረር

ወርቃማይቱ ጀንበር ( ደበበ ሰይፉ) 

ይርጋለሜ ነይ ነይ ይርጋለም

የጠፋሽዉ ተይ ነይ ግዴለም

ከእንግዲህ ወዲያ ጨዋታ የለም

ከእንግዲህ ወዲያ መተከዝ የለም ( አብርሃም ረታ)

እምዬ ይርጋለም የኔ መልከ ቀና፣

የጥንቱ ውበትሽ ትውስ ይለኝና፣

ከአቻዎችሽ  ጋራ አስተያይሽና ፣

እንዴት ብትወዳት ነዉ  ጌታን እለውና፣

ስደነቅ አድራለሁ ባደለሽ ቁንጅና !!!

“ውሰደኝ መልሰኝ አንተ መንታ መንገድ ፣

በይርጋለም ናፍቆት ጨርቄን ጥዬ ሳላብድ!”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *